17/06/2026
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በእዣ ወረዳ የቪታሳሉቲ የብረት ፋብሪካን መርቀው ከፈቱ!!
⠀
•• Gurage Tv - ሰኔ 08/2018 ዓ.ም
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የቪታሳሉቲ ማኑፋክቸሪንግ የብረት ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቆ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተመርቋል።
⠀
የሀሮት ሪልስቴት እህት ኩባንያ የሆነው ይህ ፋብሪካ በ2 ሺህ 550 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ የተለያየ መጠንና ደረጃ ያላቸው የብረት ምርቶችን ለኮንስትራክሽን ዘርፍ በማቅረብ በሀገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የገበያ ክፍተት ለመሙላት የበኩሉን ሚና ይጫወታል።
⠀
አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ረገድ ተጠቃሽ የሆነው ይህ ግዙፍ ፋብሪካ፣ ወደ ማምረት መሸጋገሩ በአካባቢው ያለውን የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያነቃቃ ሲሆን፣ ለ273 ዜጎችም በቋሚነትና በጊዜያዊነት ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል ተብሏል።
⠀
በዞኑ የተፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት አጋጣሚ በመጠቀም ባለሀብቶች በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድንና ሪል እስቴት ዘርፎች በስፋት እየተሰማሩ ሲሆን፣ ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
⠀
የአካባቢውን ሁለንተናዊ የልማትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማገዝ የተጀመሩ የግል ኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችና መሰል የፋብሪካ ማስፋፊያ ጥረቶች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።