16/07/2026
ጋር Instagram – ከእነሱ ዋና አድናቂዎች እንደ አንዱ ሆኜ አሁን እውቅና አግኝቻለሁ!የሰነድ አለመኖር የካሳ መብትን ያሳጣልን?
***********
ለመሆኑ አንድ ግለሰብ ለአሥርተ ዓመታት የቆየ ይዞታ እያለው፣ ይዞታውን የሚያረጋግጥ "የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ወይም ደብተር" ስለሌለው ብቻ ያለ ካሳ ከመሬቱ እንዲፈናቀል ሕጉ ይፈቅዳል?
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 198400 (ሐምሌ 27 ቀን 2013 ዓ.ም) በሰጠው ውሳኔ ለዚህ ጥያቄ ግልጽ ምላሽ ሰጥቷል።
የክርክሩ መነሻ
አመልካች በጅማ ከተማ ውስጥ ለረጅም ዘመን የቆየ ይዞታ ያላቸው ሲሆን፣ የከተማው አስተዳደር "ይዞታው ለሕዝብ ጥቅም ይፈለጋል" በሚል ለልማት ሲነሳ አመልካች "የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ (ካርታ) የላችሁም" በሚል ካሳ ሳይከፈል እንዲነሱ መወሰኑ ክርክሩን አስነስቶታል።
የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ
መደበኛ ፍርድ ቤቶች "አመልካች በቅድሚያ የይዞታ ማረጋገጫ ማውጣት ነበረባቸው" በሚል የሰጡትን ውሳኔ የሰበር ሰሚ ችሎቱ በመሻር የሚከተሉትን መሠረታዊ የሕግ ነጥቦች አስፍሯል፦
የሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ፦ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 40(1) እና (7) መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ በሠራው ንብረት ላይ ሙሉ መብት አለው። መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ሲል ንብረቱን በሚወስድበት ጊዜም ተመጣጣኝ ካሳ በቅድሚያ የመክፈል ግዴታ አለበት።
የሰነድ አለመኖር እና የይዞታ መብት፦ አንድ ግለሰብ ይዞታው ላይ ለረጅም ዘመን መቆየቱ እየታወቀ፣ አስተዳደራዊ በሆኑ ምክንያቶች ወይም በወቅቱ የነበሩ አሠራሮች ባለመኖራቸው ምክንያት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ባይኖረውም፣ ይዞታው ለሕዝብ ጥቅም ሲፈለግ "ሰነድ የለህም" በሚል ብቻ ያለምንም ካሳ እንዲነሳ ማድረግ የሕግ መሠረት የለውም።
የአስተዳደሩ ግዴታ፦ ይዞታው ለሕዝብ ጥቅም ሲፈለግ፣ አስተዳደሩ በቅድሚያ ይዞታው የአመልካች መሆኑንና ለምን ያህል ጊዜ እንደቆዩ አጣርቶ ተገቢውን ካሳ ሊከፍል ይገባል እንጂ፣ ካሳ ላለመክፈል የሰነድ አለመኖርን እንደ መከላከያ ሊጠቀምበት አይችልም።
ይህ ውሳኔ በተለይ በከተማም ሆነ በገጠር በይዞታቸው ላይ ለረጅም ዘመን የቆዩ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ (ካርታ) ያልወጣላቸው ዜጎች፣ ለልማት ሲነሱ የመካስ መብታቸውን የሚያስከብር ነው።
#መላኩ ፍቃዱ